ሰበር ዜና ቀሲስ ሳሙኤል ብርሃኑ ሥልጣነ ክህነታቸው ታገደ (ተያዘ)

(አደባባይ ሚዲያ የካቲት 25/2012 ዓ.ም፤ March 4/2020)፡- በዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀ/ስብከት ሥር በዝርወት ባለችው የደ/ሰ/ቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩትና «ኦሮሞ በመሆኔ ተገፋሁ» በሚል ምክንያት አዲስ የኦሮሞ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አቋቁማለኹ በሚል እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ቀሲስ ሳሙኤል ብርሃኑ ክህነታቸው መያዙ ታወቀ።

በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የተጻፈውና ለአደባባይ ሚዲያ የደረሰው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ቀሲስ ሳሙኤል በአካል ቀርበው ሐሳባቸውን ግልጽ እንዲያደርጉ የቀረበላቸውን ተደጋጋሚ የቃል እና የጽሑፍ መልእክት ባለመቀበላቸው በመጨረሻ የተሰጣቸው የአስር ቀን ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው ክህነታቸው የተያዘው።

ቀሲስ ሳሙኤል ክህነታቸው ከተያዘ በኋላ በክህነት አገልግሎት የሚቀጥሉ ከሆነ ደግሞ እስከ መወገዝ ሊደርሱ እንደሚችሉ የብፁዕነታቸው ደብዳቤ አበክሮ ያስረዳል። (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል)
————–
ለ ቀሲስ ሳሙኤል ብርሃኑ
ጉዳዩ ሥልጣነ ክህነትዎ መያዙን ይመለከታል

ከላይ በርዕሱ እንደተገለጸው ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ተቋቁሟል ስለተባለው ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ስለመነጋገር በቁጥር ሀ/ሰ/417/12 በተጻፈ ደብዳቤ አሳውቀናል። በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ተደርጓል። በመቀጠል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በሚል በቁጥር ሀ/ሰ/417/32 በተጻፈ ደብዳቤ እስከ የካቲት 22/2012 ዓ.ም በአካል መጥተው እንድንወያይ እድል ተሰጥቷል። ሆኖም ይህ ሁሉ እድል ተሰጥቶ ለመነጋገር ፍቃደኛ አይደሉም። ስለዚህ በተሰጠው ቀን ገደብ ባለመቅረብዎ በፍትህ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት በአንቀጽ አንድ ቁጥር ሁለት “ያለ ኤጲስ ቆጶስ ትዕዛዝ ቤተ ክርስቲያን አይስሩ፤ አንድ ሰው ስንኳ ደፍሮ ከዚህ ውጪ ቢሰራ በውስጥዋ እስከ ዘላለም ቁርባን አይቁረብ፣ ቄሱም ይህን ተላልፎ በውስጥዋ ቁርባን ቢቆርብ ይሻር።” እንዲሁም በአንቀጽ ስድስት ቁጥር 228 “ቄስ ወይም ዲያቆን ኢጲስ ቆጶስ ጳጳሱን ቢንቀው፣ ብቻውንም ቤተመቅደስ ቢሠራ፣ ሶስት ግዜ ቢጠራው መልስ ባይሰጥ እርሱ ከማዕረጉ ይሻር፣ ተከታዮቹም ይሻሩ” በሚለው ቀኖና መሠረት ታዛዥ እና ሕግ አክባሪ ሆነው ባለመገኘትዎ ሥልጣነ ክህነትዎ ተይዟል።

ይህ ደብዳቤ ከተጻፈበት ቀን ጀምሮ ማንኛውም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከመፈጸም የታገዱ መሆኑን እያሳወቅን በድፍረት የክህነት አገልግሎት ቢሰጡ ቀኖናው ከክህነት እስከ መሻር (ውግዘት ) የሚያደርስ መሆኑን ተገንዝበው በይቅርታ እና በንስሐ እንዲመለሱ ከወዲሁ እናሳስባለን።

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን
አባ ፋኑኤል
የዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት
ሊቀ ጳጳስ
(ፊርማ)

Comments are closed.