የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ። ( አደባባይ ሚዲያ መጋቢት 16/2012ዓ,ም)

በመላው ዓለም የተከሠተውን እና በቅርቡ ወደ አገራችን የገባውን ኮቪዲ- 19 ኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል ከመጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን ገለጠ።

በማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመው ግብረ ኃይል በመንግሥት እና በቤተ ክህነት ከተቋቋሙ ግብረ ኃይሎች ጋር በመተባበር እንደሚሠራና የትኩረት ቦታዎቹም አብያተ ክርስቲያናት ገዳማት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች እና የጸበል ቦታዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

የበሽታው ስርጭት እንዳይባባስ በቅዱስ ሲኖዶስና በጤና ጥበቃ ሚንስትር የተላለፈውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ፣በጸሎት ፈጣሪን መማጸን እንደሚያስፈልግ ያስገነዘበው ግብረ ኃይሉ ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ግንዛቤ ለመጠር በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ተከታታይ የግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርት እየሰጠ መሆኑንም ተናግሯል።

ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠትም ሆነ የተከሠተውን ወረርሽኝ ተከትሎ ሌሎች ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ተናቦ መሥራት፣ ከራስ ዐልፎ የተጎዱትን ለመደገፍ መዘጋጀት እንደሚገባ የተቋቋመው ግብረ ኃይል አስታውቋል።

የዜናችን ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን

Comments are closed.