የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ከቤት ሆነው እንዲሠሩ የሚንስተሮች ምክርቤት ወሰነ። (አደባባይ ሚዲያ መጋቢት 15/2012ዓም)

የዜናው ምንጫችን የጠቅላይ ሚንስተር ፅህፈት ቤት ነው

የኢትዮጵያ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ቀጥሎአል።

ዛሬ መጋቢት 15/2012 ዓም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከነገ መጋቢት 16/2012 ዓም ጀምሮ የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲያከናውኑ ወስኗል፤ ይህ አሠራር ተጨማሪ ውሳኔ እስከሚተላለፍ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ከቤታቸው ሆነው የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች በእያንዳንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አማካኝነት በሚወጣ ደንብ የሚለዩ ሲሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ለሠራተኞቻቸው ማን ከቤት ሆኖ እንደሚሠራ የሚያስታውቁ ይሆናል።

በዚህ ወቅት ከቤታቸው ሆነው የሚሠሩ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አስተዋፅኦዋቸውን ለሚፈልጉ ሥራዎች ዝግጁ እና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የሚወጡ መሆን ይኖርባቸዋል።

ይህ ውሳኔ የተወሰነው በመላው አዲስ አበባ የሚካሄድ እንቅስቃሴን እና የትራንስፖርት ዘርፉን መጨናነቅ ለመቀነስ ታስቦ ነው።

Comments are closed.