የጎጤ ቤተ ክህነት ተቃርኖ (በዮሐንስ መኮንን)

የዘውግ ቤተ ክህነትና በቋንቋ መገልገል ሁለት የሚቃረኑ ነገሮች ናቸው፡፡ የጎሳ ቤተ ክህነት የፖለቲካ ጥያቄ ሲሆን በቋንቋ መገልገል ግን የድኅነት ጥያቄ ነው፡፡ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በወላይትኛ፣ በሶማልኛ፣ በአፋርኛ ወዘተ… የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማግኘት የአማኙ ክርስቲያናዊ መብት፣ የቤተ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ ደግሞ ግዴታ ነው፡፡

እንደ ክርስትና ይህ የሚደረገው ለፖለቲካዊ መብት ወይም ለማንነት ግንባታ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ወንጌልን በሚገባ ሰምቶ ለማመን እና አምኖም ለመጽደቅ እንዲችል ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” (ሮሜ. 10:14) እንዳለው። ለመስማት ደግሞ በሚሰሙት ቋንቋ መማር ማስተማር የግድ ነው፡፡

በነገራችን ላይ፣ በክርስትና ትምህርት፣ ‘ሰው በሚገባው ቋንቋ መማር አለበት’ ማለት የግድ በብሔሩ ቋንቋ ላይሆን ይችላል፡፡ በሚረዳበት ቋንቋ ማለት ነው፡፡ የቋንቋው ዋና ዓላማ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ‹እንዲሰማ› ነው፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በአኩስም ስትቋቋም የአገልግሎት ቋንቋዋ ግሪክኛ ነበር፡፡ ግሪክ የአኩስማውያን የብሔር ቋንቋቸው ሳይሆን የሥራና የንግድ ቋንቋቸው ስለነበር ነው፡፡ በክርስትና የቋንቋ ዓላማ ወንጌልን በሚረዱት ቋንቋ ለማስተላለፍ ነው፡፡

ይህን አገልግሎት ለመስጠት ግን የዘውግ ቤተ ክህነት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለምን?

የዘውግ ቤተ ክህነት የፖለቲካ እንጂ የሃይማኖት ጥያቄ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ያለባት ክርስቲያናዊ ጥያቄን እንጂ ፖለቲካዊ ጥያቄን አይደለም፡፡ በአንድ አካባቢ ለማገልገል የአንድን አካባቢ ቋንቋ መቻል እንጂ የአንድ አካባቢ ተወላጅ መሆን ለክርስትና መሠረታዊ አይደለም፡፡ ሐዋርያት ሁሉም የእሥራኤል ተወላጆች ናቸው፡፡ በመላው ዓለም ተዘዋውረው ያስተማሩት የየሀገሩ ቋንቋ ተገልጦላቸው ነው፡፡ ጌታችን ከየሀገሩ ሐዋርያትን አልመረጠም፤ በየሀገሩ አሠማራ እንጂ፡፡ ነገር ግን ሕዝብ በሚያውቀው ቋንቋ እንዲያስተምሩ ቋንቋ ገለጠላቸው፡፡

በሕዝቡ ቋንቋ ማስተማርና የጎሳው አባል መሆን የተለያዩ ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ያስተማሩት እነ አቡነ ሰላማ፣ ተሰዓቱ ቅዱሳን፣ ማኅበረ ጻድቃን፣ አባ ሊባኖስ፣ እጨጌ ዕንባቆም፣ ወዘተ. የሕዝቡን ቋንቋ ለምደው በሕዝቡ ቋንቋ አስተማሩ እንጂ ብሔረሰብ አልቀየሩም፡፡

ቤተ ደብረ ሊባኖስ በጎንደር ከ200 ዓመታት በላይ ሲቆይ ከነበሩት እጨጌዎች መካከል ከ7 በላይ የኦሮሞ ልጆች ተሾመዋል፡፡ እነዚህ አባቶች በጎንደር ከተማ ጠቅላላዋን ቤተ ክርስቲያን ያስተዳደሩት ጎንደሬ ስለሆኑ አይደለም። ክርስቲያን ስለነበሩ እንጂ፤ የቤተ ክርስቲያዋን ትምህርት ተምረው ብቁ ስለሆኑ እንጂ፤ አቡነ ጴጥሮስ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ የሆኑት የምሥራቅ ኢትዮጵያ ተወላጅ ስለሆኑ አልነበረም፡፡

የአምቦ ተወላጅ የሆነው ታላቁ ባለ ቅኔ፣ ጸጋዬ ገብረ መድኅን የአቡነ ጴጥሮስ የመጨረሻ ሰዓት በምናቡ ተመልክቶ እንደገጠመው

ስሜን በስምሽ ሰይሜ፣
ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም፣
ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣
በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ፤

ማንኛውም የኦሮሞ ተወላጅ ለዋዜማ ግሼን ማርያም፣ ለክብሯ ደብረ ሊባኖስ እንዳይሄድ ማድረግ፤ የሁሉ አባት በሚሆንበት በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ ወንበር እንዳይቀመጥ አግዶ በብሔር የፖለቲካ ወንበር መጥመድ ነው፡፡ የብሔረሰብ ቤተ ክህነት ዓላማው ይህ ነው፡፡ ክርስያንን ከመንፈሳዊ ዕድገት መግታት፡፡ ለዚህ ነው አጥብቀን የምንቃወመው፡፡ ክርስቶስ በደሙ ያፈረሰውን ግንብ በፖለቲካ በኩል በወንድሞቻችን ላይ ስለሚገነባ፡፡

ማንኛውንም ወገን በክርስትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዳያደርግ የሚከለክል ልማድ፣ ባህል፣ አሠራር መኖር የለበትም፡፡ ልክ ግብጻውያን ኢትዮጵያውያን ከጵጵስና እንደ ከለከሉበት ዓይነት፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከየትኛውም ብሔር ቢመጣ ምእመን፣ ዲያቆን፣ ቄስ፣ ጳጳስ፣ ፓትርያርክ እንዳይሆን የሚከለክል ቀኖና የለም፡፡ እንኳን ኢትዮጵያዊው የመናዊው ዕንባቆም ትልቁን የደብረ ሊባኖስ እጨጌነት ደርሶበት ነበር፡፡ በልማድ ግን ያልተፈቱ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች የሚፈቱት ቀኖናውን በማስከበር፣ ልማዱን በመሻር ብቻ ነው፡፡

ዘውጌ ቤተ ክህነት የአማኞችን ሱታፌ ይገድባል፡፡ አንድ ሰው ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ሌሎች ማንነቶቹ ሁለተኛ ናቸው፡፡ አንድ የሚሆነው በክርስቶስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናዊ ሁለገብ ዕውቀት፣ ቤተ ክርስቲያናዊ ቋንቋና ቤተ ክርስቲያናዊ ንጽሕና ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ ምእመን ለፓትርያርክነት እንዳይበቃ የሚያደርገው ምንም ክልከላ የለም፤ ከራሱና ከታሪክ በቀር፡፡ ለዚህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ሁለገብ ትምህርት መማር አለበት፡፡ ለዚህ ትምህርት አንዱ መሠረት ግእዝ ነው፡፡

ግእዝ ዛሬ የማንም ብሔረሰብ ቋንቋ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ቋንቋዋ ነው፡፡ ለዚህ ነው የዓለም ሊቃውንት ‹Ethiopic› ብለው የሚጠሩት፡፡ ከየትኛውም ማኅበረሰብ የመጣ አገልጋይ ከራሱ ቋንቋ በተጨማሪ ቢያንስ ግእዝን ማወቅ አለበት፡፡ የጋራ ቋንቋ ስለሆነ፡፡ ዘውጋዊ ቤተ ክህነት ግን አንድን ምእመን ከራሱ ጎሳ ውጭ እንዳያገለግል የሚገድብ ነው፡፡

በጥንቷ ኢትዮጵያ ዓረብኛ ቋንቋ በደብረ ሊባኖስና በጎንደር ደብረ ማርያም ይሰጥ ነበር፡፡ ለምን? በአንድ በኩል ብዙ ድርሳናት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ ስለተተረጎሙ፣ በሌላ በኩል ከግብጽ፣ ሶርያ፣ ኢየሩሳሌም ጋር የነበረን መንፈሳዊ ግንኙነት በዓረብኛ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ ኢየሩሳሌም ለሚጓዙ ተሳላሚ መነኮሳት አስፈላጊ በመሆኑ፡፡ በዚህ የተነሣ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ግእዝና ዓረብኛን ተጠቅመው በግብጽ፣ በሶርያና በሊባኖስ ገዳማት እስከ አበ ምኔትነት ደርሰው አገልግለዋል፡፡

ዛሬም እንድ የኦሮሞ፣ የወላይታ፣ የትግራይ፣ የአፋር፣ የሶማሌ ወዘተ ምእመን አባት እንዳይሆን መከልከል የለብንም፡፡ አባትነቱ ደግሞ የሁሉም አባት ነው፡፡ በሀገር ውስጥ በየትኛውም ሀገረ ስብከት ሊያገለግል፣ የትኛውንም ደብርና ገዳም ሊያገለግል ይገባዋል፡፡ መብቱም ነው፡፡ የማኅበረ ሥላሴ፣ የጣና ገዳማት፣ የገርዓልታ ገዳማት፣ የደብረ ሊባኖስ፣ የጎባ ተክለ ሃይማኖት፣ የምሑር ኢየሱስ፣ የላሊበላ፣ የአኩስም ጽዮን፣ የቂልጡ ካራ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የዋልድባ መነኮስና አበ ምኔት እንዳይሆን መታገድ የለበትም፡፡ ከዚህም አልፎ የኢየሩሳሌም ገዳማት ራኢስ፣ በመላው ዓለም የተበተኑ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይና አስተዳዳሪ እንዳይሆነ መታገድ የለበትም፡፡

ዘውጌያዊ ቤተ ክህነት የክርስቲያኖችን ዕድል አጥብቦ የጎጥ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠርቱ (Ethnic Church) በማስገደድ መንፈሳዊ ቅንጨራ ያስከትላል፡፡

ለዚህ ነው በቋንቋ መጠቀምና የዘውጌ ቤተ ክህነት ሁለት የተለያዩ ብቻ ሳይሆኑ የሚቃረኑ ሐሳቦች የሚሆኑት፡፡

በብዙ ቋንቋ መገልገልና ማገልገል የሚበረታታ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በማሠልጠኛዎቿና በኮሌጆቿ ይህንን ማበረታታት አለባት፡፡ የተለያዩ የሀገራችንንና የውጭ ቋንቋዎችን በማሠልጠኛዎች መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያዊነት ስለሆነ፡፡ እነዚያ ቋንቋዎች መማር ያለባቸው ግን አፍ የፈቱባቸው ሰዎች ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡ አማርኛ የሚናገረው ኦሮምኛና አፋርኛ፣ ትግርኛ የሚናገረው ወላይትኛና ሲዳምኛ፣ ኦሮምኛ የሚናገረው ሶማልኛና ጉምዝኛ ወዘተ እንዲናገር ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ዓላማችን አጥር መሥራት ሳይሆን በክርስቶስ ማገናኘት ነውና፡፡

ለዚህ ግፊትም ጥረትም ትብብርም እናድርግ፡፡ ዋና ዓላማችንም ሁሉም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የጸጋዋ ተካፋይ ከመሆን በቋንቋ ምክንያት እንዳይታገዱ ዕንቅፋቱን ማንሣት ነውና፡፡

ከዚህም ባሻገር በብዙ ቋንቋዎች የሚያገለግሉ አገልጋዮች ማፍራት ነው፡፡ በኦሮምያ ለማገልገል ግእዝና ኦሮምኛ መቻል እንጂ ኦሮሞ መሆን የግድ አይደለም፡፡ በአማራ ክልል ለማገልገል ግእዝና አማርኛ መቻል እንጂ አማራ መሆን የግድ አይደለም፡፡ በሌሎችም እንዲሁ፡፡

ከኤርትራ የሚወለዱት ኤዎስጣቴዎስ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከጎጃም የተወለዱት አብራንዮስ በኤርትራ አገልግለዋል፡፡ ከሮም የመጡት አቡነ አረጋዊ እስከ ዐርባ ምንጭ፣ ከግብጽ የመጡት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ አስተምረዋል፡፡ ወላይታ የተወለዱት አባ ኤልሳዕ ደብረ ሊባኖስ መጥተው እጨጌ ሆነዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ሐዋርያዎቹ የአካባቢ ተወላጅ ስለሆኑ አልነበረም፡፡ የጋሞው አባ ባሕሪይ በጎንደር ቤተ መንግሥት ባለሟል የሆኑት ጎንደሬ ስለነበሩ አይደለም፡፡ ለአገልግሎት መንፈሳዊ ዕውቀትና የማስተማሪያ ቋንቋ እንጂ ብሔረሰባዊ ማንነት ከክርስትና ጋር አይያያዝም፡፡

የጎጥ ቤተ ክህነት ቤተ ክርስቲያንን የማፍረሻ የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆን በቋንቋ ማስተማርና መማር ግን መንፈሳዊ መብት ነው፡፡ “በቋንቋ መማር እንጂ በቋንቋ መካድ መንፈሳዊነት አይደለም”

Comments are closed.