ፖሊስ ሌሊቱን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ ባደረገው ጥረት ሁለት ሰዎች ተገደሉ፣ የጅምላ አፈሳ ተካሒዷል

(አደባባይ ሚዲያ፣ ጥር 26/2012 ዓ.ም፤ Feb. 4/2020)፡- አዲስ አበባ 22 መንገድ፣ ቅዱስ ገብርኤልን ሆስፒታል አካባቢ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ጎን ካለው ክፍት ቦታ ላይ ለብዙ ዓመታት ክፍት የነበረ ቦታ የተሠራ ቤተ ክርስቲያንን በሌሊት ለማፍረስ በተደረገ ጥረት ሁለት ክርስቲያኖች ተገደሉ።

ስለ ጉዳዩ እማኝነታቸውን ያቀረቡት ጋዜጠኞቹ ሀብታሙ ምናለ እና ብርሃኑ ተ/ያሬድ እንደጻፉት ከሆነ «ዛሬ /ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ/ ሌሊት 7:00 ሰዓት (1AM) ሲሆን አድማ በታኝ ሌሊት ኃይል በመጠቀም ለማስለቀቅ ከመሞከር ባለፈ አስለቃሽ ጭስ ሲጠብቁ በነበሩ እናቶች፣ ወጣቶች እና የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ልጆችም ጭምር ላይ» መወርወሩን እንዲሁም ጥይት መተኮሱንና ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ጋዜጠኛ ሀብታሙ እንደመሰከረው ከሆነ 22 አካባቢ ሰዎች በጅምላ መታፈሳቸው ታውቋል። ጋዜጠኛ ብርሃኑ በበኩሉ እንዳለው «ድሆች ቆጥበው የሰሩትን ኮንዶሚኒየም ወርሮ የያዘ ዱርዬን ማስለቀቅ አቅቶት ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ መግለጫ የሚሰጠው መንግሥት፣ “የመሬት ወረራ በአዲስ አበባ ላይ ተጧጡፏል እርምጃ ልወስድ ነው” ካለ በኋላ “ትቼዋለሁ ውረሩት” ያለው መንግሥት» የኦርቶዶክስ ጉዳይ ሲሆን እንዲህ የኃይል ርምጃ መውሰዱ ሲታይ ዓላማው «ሕገ ወጥ ቤት ማፍረስ» ሳይሆን «ቤተ ክርስቲያንን ማዋረድ» እንደሆነ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል ብሏል።

«በቤት ለቤት አፈሳ ብዙ ምእመናን ተግዘዋል፤ የአለቆችን ፈቃድ ከመፈፀም የዘለለ ስለ ጉዳዩ እውቀት የሌላቸው ወታደሮች ቅዱስ ታቦቱን መውሰድ አለብን የሚል ድፍረት ላይ ናቸው። የተያዘው ኦርቶዶክሳውያንን ማጥቃትና ቤተክርስቲያንን ማዋረድ ነው። ከመሬት ወረራ ጋር አታመሳስሉት» ሲል አክሏል ጋዜጠኛ ብርሃኑ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው እሑድ «ጋርመንት» በሚባለው አካባቢ “መስጅድ ለመሥራት” ብለው በአንድ ጀንበር ሰፊ ቦታ የያዙ ሰዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ምንም ዓይነት እርምጃ አለመወሰዱ ይታወቃል።

Comments are closed.