የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እየገባ መሆኑ ተነቀፈ

(አደባባይ ሚዲያ፣ ጥር 26/2012 ዓ.ም፤ Feb. 3/2020)

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት መቀጠሉ አማኞቿን በማስቆጣት ላይ እንደሚገኝ አንድ ከፍተኛ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኃላፊ አስታወቁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መልአከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት «የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ በአንዳንድ ቦታዎች የሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና የሕግ ከለላ ያለመስጠት የቤተ ክርስቲያኗን ተቋሟዊ ህልውና ከመጋፋቱም በላይ አማኞቿን በእጅጉ እያስቆጣ ነው» ብለዋል።

በሀገሪቱ አዲስ የለውጥ አየር ነፍሷል ከተባለ እና በኦዴፓ መሪነት አዲስ የአስተዳደር መሠረት ከተጣለ ወዲህ በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ፣ የምእመናን መገደልና መፈናቀል፣ የካህናት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል እና የክርስቲያኖች ንብረት መውደም በመካሔድ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህም የዜጎችን መብት ያስከብራል ተብሎ የሚታሰበው የክልሉ ፖሊስ ለጥቃት አድራሾች ከለላ ከመሆን አልፎ በቀጥታ በወንጀሉ ሲሳተፍ እንደነበር ብዙ ማስረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ። መንገድ በሚዘጋባቸው እና በኦርቶዶክስ በዓላት ላይ ድንጋይ በሚወረወርበት ወቅት የፖሊስ አባላት እጃቸውን አጣምረው ወንጀሉን እንደ ድራማ ሲመለከቱ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች በብዛት ተለጥፈው ይታያሉ።

ጉዳዩ መስመር በመሳት ላይ መሆኑን የተመለከቱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ኃላፊ «ይህ አድራጎት የከፋ መልክ ሳይዝ አፋጣኝ እልባት እንዲያገኝ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል» ሲሉ በአጽንዖት አሳስበዋል።

Comments are closed.