«ጥምቀት» ዓለማቀፋዊ ቅርስ ሆነ ————————————–

(አደባባይ ሚዲያ፤ Dec 12/2019):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የሆነው የጌታችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀቱ በዓል ትውፊታዊ አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) ጥበቃ ከሚደረግላቸው የማይዳሰሱ የሰው ልጆች ቅርሶች ተርታ መመዝገቡ ታወቀ።

ከዚህ ቀደም ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረው እውነተኛው ዕፀ መስቀል መገኘትን በማሰብ የሚከበረው የመስቀል በዓልን ጨምሮ ዓለማቀፋዊ እውቅና ካገኙት ከፊቼ ጨምበላላ እና ከገዳ ሥርዓት ጋር መሳ ለመሳ ሆኗል – ጥምቀት።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) ያስመዘገበቻቸው የቅርሶች ብዛት 13 የደረሱ ሲሆን በዚህ ቁጥር ቅርሶቿን በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ መሆን ችላለች። የሚዳሰሱ ቅርሶች ተብለው የተመዘገቡት 1) የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ 2) አክሱም፤ 3) የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፤ 4) የአጼ ፋሲል ግቢ፤ 5) የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፤ 6) የታችኛው የኦሞ ሸለቆ፤ 7) የጢያ ትክል ድንጋዮች፤ 8 ) የሐረር ጀጎል ግምብ እና ከተማ፤ 9) የኮንሶ ባህላዊ እርከን ሲሆኑ የማይዳሰሱት ቅርሶች ደግሞ 10) የመስቀል በዓል፤ 11) ፊቼ ጨምበላላ፤ 12) የገዳ ሥርዓት እና 13) የጥምቀት በዓል ናቸው።

ቀስ በቀስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ተቀብራ ከተቀመጠችበት መቃብር እየወጣች ይመስላል። እንኳን ደስ ያለን።

Comments are closed.