ቦሌን እንደባሌ፤ * የከሸፈው የቦሌ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጥቃት ሙከራ

—————————-
* በሙዳየ ምጽዋት ውስጥ የተገኘው የማስጠንቃቂያ ጽሑፍ ምን ይላል?
* ደብሩ የፀጥታ ሥጋት እንዳለበት አሳውቆ ነበር።
* 6 የሰንበት ተማሪዎች ተጎድተዋል።
—–
(አደባባይ ሚዲያ፤ 11/30/2019)፡- በቦሌ ደብረ ምሕረት የቅዱስ ሚካኤልና ጻድቁ አባ ጎርጎርዮስ ቤተ ክርስቲያን በኅዳር 15/ 2012 ዓ.ም በሕዝባዊ ቄሮ ስም የተደራጁ ወጣቶች ባደረጉት የማጥቃት ሙከራ በሰንበት ተማሪዎች እና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ሲል የሰንበት ትምህርት ቤቱ ፀሐፊ ወጣት ሀብታሙ ምናለ ለአደባባይ ሚዲያ ገልጿል::

ወጣት ሀብታሙ እንደሚለው ከሆነ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ስጋት ላይ እንደነበር እና የደብሩ አስተዳደርም ስለ ሥጋቱ በተደጋጋሚ ለአካባቢው ፖሊስ ማሳወቁን አያይዞ ተናግሯል። የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንደነበር የገለጹት ሌሎች በቤተ ክርስቲያኑ አካባቢ የሚገኙ ምንጮች በበኩላቸው በአቅራቢያው ይኖሩ የነበሩ ምእመናን በየጊዜው በሚደርስባቸው ማስፈራሪያና ጫና የተነሣ ቤታቸውን በመሸጥ የመኖሪያ ሥፍራ መቀየራቸውን ያስረዳሉ።

በቄሮ ስም የተደራጁ የተባሉት ወጣቶች ከዚህ በፊትም ቤተ ክርስቲያኑን እናቃጥላለን በሚል መዛታቸውን ምንጮቹ አክለው አስታውቀዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ውጥረት እና ጥርጣሬ ተሞልቶ ወራትን ያስቆጠረው የቦሌ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 12 የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓልን ካከበረ በኋላ ግን ሲፈሩት የነበረው ነገር ሁሉ ሥጋ ለብሶ ገጥሟቸዋል። ኅዳር 15 ለበዓሉ ማድመቂያ የሰቀሉትን የኢትዮጵየ ሰንደቅ ዓላማ እያወረዱ በነበሩ ወጣቶች ላይ ድንገት ከበባ ይጀመራል። ወጣት ሀብታሙ እንደሚለው ከበባው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጭቅጭቅ እና መገፋፋት ያመራል።

ከዚያም በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ተሰቅለው የነበሩትን ሰንደቅ-ዓላማዎችን እያወረዱ በነበሩት አቶ መስፍን በዳዳ፣ መለሰ ፈይሳ፣ ቶማስ መኮንንና ዳዊት ደጀኔ አበበ ላይ ማስፈራሪያዎችን እና ዛቻዎችን አድርገዋል። ጥቂት ቆይቶም ከ20 በላይ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ያልሆኑ ወጣቶች ቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑን ጥሰው በመግባት ጥቃት መጀመራቸውን ምንጮቹ ያስረዳሉ።
ችግሩ እያየለ መምጣቱን የተረዱት የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ድንጋይ መወርወር የጀመሩትን ወጣቶች ይዘው ለፖሊስ ለማስረከብ ሞክረዋል። ይሁን እንጅ ፖሊስ የቤተ ክርስቲያኑን አጥር ጥሰው የገቡትን ሰዎች በቁጥጥር ሥር ከማዋል ይልቅ በነጻ መልቀቃቸውን ተከትሎ የሰንበት ተማሪዎቹ ስጋት እንደገና ይጨምራል።
የአካባቢው ፖሊሶች ሰንበት ተማሪዎቹ ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ቢገፋፉም ዓይናችን እያየ ቤተ ክርስቲያናችን ለእሳት ጥለን አንሄድም በማለት እዛው መቆየትን ይመርጣሉ። ይኽ የፖሊሶች እና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ውዝግብ አድጎ ነፍስ እስከማጥፋት የሚደርስ ርምጃ በፖሊስ መወሰድ ተጀመረ። በዚህም አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ ሦስት ወጣቶች ደግሞ ከባድ ጉዳት አስተናግደዋል። ሦስት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ያመክታል። በአሁኑ ሰዓት አካባቢው በከፍተኛ ጥበቃ ላይ ቢሆንም ስጋቱ ግን አሁንም አልተቀለለም ተብሏል።

Comments are closed.