“ሰላምንም አደርጋለሁ፤ክፋትንም አመጣለሁ” ትን.ኢሳ.45፤7።

(መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና እንደጻፉት)
የሰዎች ልጆች ክፉ ሥራ በምድር ላይ እየበዛ፣ የልባቸው ዐሳብ ምኞትም ሁል ጊዜ ፍጹም ክፉ እየሆነ በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔር ያዝናል፤ በዚህም የተነሳ መቅሰፍት በምድር ላይ በሚኖሩ ክፉ አድራጊዎች ላይ ይታዘዛል። እግዚአብሔር ክፉ ነገርን በሰው ልጅ ላይ የሚያመጣው ህልውናውን ለማሳወቅና ክፉዎች ከክፋታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነው። “በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤ ተመለሱ፣ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤ ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደሆነ አሰቡ” ተብሎ እንደተጻፈ (መዝ.77፤34)።

የእግዚአብሔር መቅሰፍት በምድር ላይ በታዘዘ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ኖኅና ሎጥ ሞገስ ያገኙ መቅሰፍቱ እንዳያገኛቸው አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተነገራቸውን ሊያደርጉ የሚገባቸውን በማድረግ የመአቱን ጊዜ በረድኤቱ ጥላ ሥር ተጠልለው ያሳልፋሉ።

በመቅሰፍት ጊዜ የእግዚአብሔር ሰዎች ከመቅሰፍቱ ይድኑ ዘንድ ምን ማድረግ ይገባቸዋል?

በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘው ኖኅ መአቱ ከመምጣቱ በፊት ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ነበር። “ጌታ እግዚአብሔር ለባሪያዎቹ ለነቢያት ያልገለጠውንና ያልነገረውን ምንም አያደርግምና” በማለት ነቢየ እግዚአብሔር አሞጽ እንዳስገነዘበው (ትን.አሞጽ 3፤7) መአቱ እንደሚመጣ እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ነግሮት ነበርና፤ ኖኅና ቤተሰቦቹ ከመቅሰፍቱ የሚድኑበትን መርከብ ሰርቷል፤ ዓለማችን ታላቅ ሁከት ውስጥ እንደምትገባ መጻዕያትን የማወቅ ሀብት የተሰጣቸው አባቶች ቀደም ብሎ ሲናገሩ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። ከሚመጣው መአት ለመዳን በኖኅ መርከብ የተመሰለ ቤተ መቅደስ ሰውነታችንን በንስሐ ከኃጢአት፣ ከበደል አንጽተን በሥጋ ወደሙ ታትመን እንድንገኝ ቀድመው አሳስበውናል።

ደዌው በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ ዓለም በምጥ ጣር ውስጥ ትገኛለች። መላው የሰው ዘር በጭንቅ ማዕበል ተውጦ ባለበት በዚህ ወቅት እንደሎጥ ከመቅሰፍቱ ስፍራ ራስን ማራቅ ግድ ነው። “የሚሰማኝ ግን በተስፋ ይኖራል፥ ከክፉም ሁሉ ያለ ድንጋጤ ያርፋል” እንደተባለ (ምሳሌ 1፤33) በእግዚአብሔር ልንመካና እሱን ተስፋ ልናደርግ ”አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው?እግዚአብሔር አይደለምን“ በማለት ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረገው ቅዱስ ዳዊትን አብነት ልናደርግ ይገባል። እንዲሁም እንደ ክርስቲያን ልባሞችና ጥንቁቆች እንሆን ዘንድ ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረንን ልንፈጽም ይገባል። “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል” እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን (ምሳሌ 2፤11) አምላካችን ከክፉው ደዌ እንዲሰውረን እየጸለይን ራሳችንን ከቫይረሱ እንድንጠብቅ በባለሙያዎች የሚነገረውን ተግባራዊ ማድረግ በእግዚአብሔር አለመታመን እንደሆነ አድርጎ ከሚያስብ አእምሮ ነጻ መሆን ይገባል።

በእግዚአብሔር ጥበቃ ውስጥ የሰው ድርሻም መኖር እንዳለበት መዘንጋት የለበትም። ሕይወታችን በተአምር ብቻ የሚመራ አድርጎ የሚያሳስብ መንፈስ ካለ ልንቃወመው ይገባል። ትክክለኛው ፍኖተ እግዚአብሔር አይደለምና። ክርስቲያን የሚገባውን የእርሱን ድርሻ እየፈጸመ ከእርሱ አቅም በላይ ያለውን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ይሰጣል እንጂ ሁሉን እግዚአብሔር ይሰራዋል በሚል ግብዝነት አይገበዝም። የሚገባውን ካደረገ በኋላ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፣አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥በእርሱም እታመናለሁ። እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፥ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃል።” (መዝ.90(91)፤1-3) የሚለውን አምላካዊ ቃል በማሰብ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ማድረግ ይገባል። ከዚህ አልፎ አምላክ እንደሌላቸው አሕዛብ በጭንቀት ማዕበል ተውጦ የሚይዙትንና የሚያደርጉትን ማጣት ከክርስቲያኖች አይጠበቅም።

እግዚአብሔር መአቱን አርቆ፤ ምህረቱን ያውርድልን

Comments are closed.