ከፀሎትና ከምህላው ጎን ለጎን የህክምና ባለሙያዎችን መመሪያ መተግበር እደሚገባ ቅዱስነታቸው አሳሰቡ።

(አደባባይ ሚዲያ መጋቢት 12/2012ዓም)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከጸሎት እና ምህላው ጋር እጅን መታጠብ እና ተዛማጅ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ኮሮኖ ቫይረስ በእጅ ላይ በህይወት ሊቆይ ይችላል፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን እጅን የመታጠብ እና ንፅህናን የመጠበቅ ሥርዓት እና መንፈሣዊ ባሕል አላት፡፡ ይህም በቅዱሣት መጻሕፍትና በሥርዓተ አምልኮ ዘወትር በየጊዜው የሚፈፀም ነው፡፡ ስለዚህ እጅዎን ሣይታጠቡ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ እጅ ላይ ቫይረሱ ሊኖር ስለሚችል ሳያውቁት ዓይንን ሊያሹ፤ አፍንጫን ሊነካኩና ሌሎች መሰል ነገሮችን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ከነዚህ ድርጊቶችም ይቆጠቡ፡፡
እጅዎን ደጋግመው ሣይሰለቹ በሳሙና ቢያንስ ለ20 ሰከንድ በደንብ ይታጠቡ፡፡
እጅን መታጠብና በንጽህና መያዝ ከኮሮና ቫይረስ እና ከሌሎችም በሽታዎች ዋነኛ የመከላከያ ዘዴ ነው። እጅን መታጠብ በጣም ቀላል ተግባር ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በቤተክርስቲያን በመኖሪያ ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ ህፃናት እና አረጋውያን በሚውሉበት ቦታ እና ሆስፒታሎች አካባቢ ለመከላከል ይጠቅመናል። ንጽህ እጅ ከሰው ወደ ሰው እና በአካባቢያችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ይገታል፡፡
ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መመሪያዎችን እንተግብር።

የዘገባው ምንጭ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን መገናኛ ብዙሃን ነው።

Comments are closed.