“መምህር ምሕረተ አብ አሰፋ እንዳያስተምር ተከልክሏል።” (የአዲስ አበባ ፖሊስ)

(ጋዜጠኛ ሀብታሙ ምናለ እንደጻፈው)

በወያኔ መራሹ መንግሥት ጊዜ የእስልምና እምነት ተከታዮች በቀጥታ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን እንዳያከናውኑ ሰላምን እስከ መንሳት፣ በመንግሥት ፍቃድ መጅሊስ እስከማቋቋምና ለመንግሥት ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን ሃይማኖታዊ ቦታ ላይ እስከመመደብ ተደርሶ ነበር።

በጊዜው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች በሙሉ ለሙስሊም ወንድሞቹ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊዎች ተለቃቅመው ሲታሰሩ ሄዶ በመጠየቅ፣ በየመስጊዱ በመዞር ትግላቸውን በመደገፍ ሙስሊም ክርስቲያን ሳንል ስንዘግብ ነበር። የማልረሳው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ አንዋር መስጂድ ተገኝቶ በነበረበት ወቅት ፖሊስ እሱን ለመምታት ለጭንቅላቱ ዱላ ሲሰነዝር ራሱን ለመከላከል ሲል ላፕቶፑ መሰበሩ፣ ወይንእሸት ሞላ በፖሊስ ዱላ ጭንቅላቷ ተፈንክቶ ደም እየፈሰሳት መታሰሯ፣ አናንያ ሶሪ እኔ በምመራው «ቀዳሚ ገጽ» ጋዜጣ ላይ “የሙስሊሞች ዋይታ ከጋዛ እስከ አንዋር” የሚል ሸጋ ጽሑፍ በመጻፍ አጋርነት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ከሙስሊም ጋር በጋራ ትግል የተደረገባቸው ከትግሎች ትውስታዎቻችን መካከል ጥቂቶች ናቸው።

አሁን ደግሞ የጭቆናውና የበደል ተራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ ሆኗል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና የከፋ ያረገው እየገፏት ደጋፊ መስለው በሚታዩ የመንግሥት መዋቅር ጭምር መሆኑ ነው። (ታከለ ዑማ ጭምር) በሕወሐት ጊዜ የሕወሐትን ሴራ ቀድመው የነቁ ሰዎች በዐውደ ምሕረት ላይ ሰዎች እንዳይሰብኩ የማኅበረ ቅዱሳን አባልነት ታርጋ ተለጥፎ ይከለከሉ የነበረ ቢሆንም ይሄንን መመሪያ ወደ ጎን በመተው እንዲያስተምሩ ይደረግ ነበር።

ከለውጡ ማግስት በኋላ በጅግጅጋ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እንዲሁም በአዲስ አበባ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለው በደል እየባሰና መልኩና ቅርጹን እየቀያየረ በስፋት ችግር እየፈጠረ ይገኛል። በትላንትናው ዕለትም መምህር ምህረት አብ አሰፋ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር ፕሮግራም ተይዞ፤ ሕዝቡ በሰዓቱ ቢገኝም የቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዋና ኃላፊ ኮማንደር ወ/ሰማያት፣ የደንበል አካባቢ ማዘዣ ጣቢያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ፍጹም እንዲሁም የአካባቢው የኮሚኒቲ ፖሊስ ኃላፊ ሳጅን ኢብራሂም መምህር ምህረት አብ ወደ ቤተ ክርስቲያን ግቢ እንዳይገባ በፖሊስ መኪና የመግቢያውን በር ዘግተው “መምህር ምህረት አብ አሰፋ እንዳያስተምር ተከልክሏል” በማለት ቢያግዱም ከደብሩ አስተዳዳር መልአከ ሰላም ዓይነ ኩሉ ጋር በመሆን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በቁርጠኝነት በመከራከራቸው ከፖሊሶች “አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ እንዳያስተምር!” በማለት መመሪያ በመስጠት ገብቶ እንዲያስተምር ተደርጓል። መምህር ምህረተ አብም አስተምሮ፣ ሕዝቡም ተምሮ በሰላም ወደ ቤቱ ገብቷል። እስካሁን ባለኝ መረጃ መሠረት መምህሩ እንዳያስተምር ከቤተ ክህነትም ከሀገረ ስብከትም የተላለፈ መመሪያም ሆነ ትዕዛዝ የለም። እስካሁን ባለን ልምድ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት ብዙ ነው መዘዙ! ይሄንም ለማወቅ ሕወሐት ያለችበትን ደረጃ ማወቅ ብቻ ይበቃል፡፡

ለማሳወቅ ያህል በዛሬው ዕለትም በቦሌ ሚካኤል እንደሚያስተምር ይታወቃል።
——————
ማሳሰቢያ ከአደባባይ ሚዲያ፡-
ጋዜጠኛ ሀብታሙ ስለሰጠኸን ዝርዝር መረጃ እያመሰገንን የተወደዳችሁ የአደባባይ ቤተ ሰቦችም ነገሩን ልብ ብላችሁ እንድትከታተሉ አደራ ለማለት እንወዳለን። በዐውደ ምሕረታችን የሚቆውን መምህር የሚመርጥልን ፖሊስ አይደለም። ግጻዌአችንን የሚያወጣልን መንግሥት አይደለም። አሁንም ይህንን ትንኮሳ አቁሙ ስንል በትህትና እናሳስባለን። ይህንን የመብት ጥሰት የሰሙ የመንግሥት ኃላፊዎችም በቤተ ክርስቲናችን ላይ እየተደረገ ያለውን ሕገወጥነት አደብ እንዲያስገዙ እንጠይቃለን።

Comments are closed.