«በሀገረ ስብከቴ ምንም ዓይነት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በጥንቃቄ እየሠራሁ ነው» (ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ)

(አደባባይ ሚዲያ፤ ጥር 29/2012 ዓ.ም፤ Feb. 7/2020)፡- ራሱን «የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት አደራጅ ኮሚቴ» ብሎ የሚጠራው ቡድን ሰሞኑን በሚኒሶታ ሊያደርገው አቅዶታል ለተባለው እንቅስቃሴ «ምንም ዓይነት እውቅና አልተሰጠውም» ሲሉ የሜኔሶታ እና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ለአደባባይ ሚዲያ ገለፁ።

ከሀገር ቤት ጽላት ያሉትን በማምጣት ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት እየተንቀሳቀሱ ነው ስለተባሉት ቀሲስ በላይ መኮንን ሲገልፁም «ከእኔ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አላደረግንም። ነገር ግን የቀረበልንን የቤተ ክርስቲያን ይከፈትልን ጥያቄን በአግባቡ መርምረን ምላሽ እንሰጣለን» ሲሉ ለአደባባይ ሚዲያ ተናግረዋል::

በቅርቡ በሚዲያ ላይ «አቡነ አራርሳ» ተብለው መጠራታቸውን እንዴት ያዩታል ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም “አራርሳ እናት አባቴ ያወጡልኝ መጠሪያ ስሜ ነው። አሁን ግን ቤተ ክርስቲያን የምታውቀኝ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በሚል ነው» ሲሉም ገልጸዋል። ይሁን እንጅ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ባልተገባ መንገድ መጠቀማቸው እንዳሳዘናቸው አስታውቀዋል።

ብፁዕነታቸው ይህንኑ አስመልክተው ባሠራጩት ደብዳቤ «በቃል የቀረበላቸው» የኦሮምኛ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያን መክፈት ጥያቄ መኖሩን መግለጻቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ብፁዕነታቸው አላቸው በሚባል አቋም «የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ደጋፊ እና መሪ» ናቸው ከሚባሉት ጳጳሳት መካከል አንደኛው እሳቸው ናቸው እየተባሉ በብዙዎቹ ይወቀሳሉ።

Comments are closed.