የኦሮሚያ ብልጽግና ግምገማ ጀምሯል

* አሁንስ ስለ ክርስቲያኖች ጭፍጨፋ በሰፊው ይነጋገር ይሆን?(አደባባይ ሚዲያ፤ ነሐሴ 2/2012 ዓ.ም፤ 8/8/2020)፡- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን በመምራት ላይ የሚገኘው «የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ባጋጠመው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ግምገማ እያካሄደ» መሆኑን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በትዊተር ገጻቸው አስታወቁ። «Paartiin Badhaadhinaa Oromiyaa dhimmota tibbana naannichatti mudatan gamaaggamaa jira» ማለትም «የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ባጋጠመው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ግምገማ እያካሄደ ነው» ሲሉ አጭር የትዊተር መልእክታቸው ያስተላለፉት የፓርቲው ሊቀመንበር እና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ፓርቲው ያጋጠመው «ወቅታዊ ጉዳይ» ምን እንደሆነ ግን አልጠቀሱም።ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ አካባቢዎች በሃይማኖታቸው ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ ክርስቲያኖች ጉዳይ እንዲሁም በሕይወት ቢተርፉም ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ አጥተው፣ ከቤታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ ሁኔታዎች በስቃይ ላይ ስለሚገኙት ዜጎች ክልሉ እስካሁን ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ ሳይሰጥ ቆይቷል። በነፍሰ ገዳዮች ሕይወቱ የተቀጠፈውን አርቲስት ሐጫሉ ሑንዴሳን በተመለከተ ሐዘናቸውን የገለጹት የክልሉ ፕሬዚዳንት ሺመልስ አብዲሳ በተመሳሳይ ምክንያት ስለተጨፈጨፉት ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ሐሳብ ሳያካፍሉ ዝምታን መርጠዋል።ክልሉ የክርስቲያኖችን መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ በዝምታ ባለፈበት ሁኔታ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ስለ ጭፍጨፋው የሚዘግቡ ሚዲያዎችን እና ስለ ጉዳዩ የሚያነሡ ፓርቲዎችን በጽኑዕ አስጠንቅቀዋል።የብልጽግና ፓርቲ ሊቀ መንበር እና ከኦሮሚያ ክልል የተገኙት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይም በመግለጫ መካከል «ሰዎች ይታረዳሉ» በማለት ከመግለጻቸው ባለፈ እስካሁን ስለጉዳዩ የተናገሩት ነገር የለም። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ጠ/ምኒስትሩም ሆኑ የክልሉ ፕሮዚዳንት ተጎጂዎችን ለመመልከት ወደ ቦታው አልሄዱም። በዚህ መጠነ ሰፊ ጥቃት የክልሉ ሁለት ትልልቅ ከተሞች ዝዋይ እና ሻሸመኔ የጦርነት ዐውድማ የመሰሉ ሲሆን የክርስቲያኖች ንብረቶች ናቸው የተባሉ ታላላቅ ሀብቶች ከፍተኛ ውድመት ተፈጽሞባቸዋል። የአካባቢው የጸጥታ ኃይል ውድመቱ ሲፈጸም በዝምታ በመመልከት «አልታዘዝንም» የሚል ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል።

Comments are closed.