በዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ስር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አገልግሎታቸውን ለጊዜው ከየካውንቲው በሚወጡ መመሪያዎች መሠረት እንዲያስተካክሉ መመሪያ ተላለፈ

** ካህናትና ምእመናን ይህን ክፉ ጊዜ በየቤታቸው በጾምና በጸሎት እንዲያሳልፉ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ- ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል አሳሰቡ፣
(አደባባይ ሚዲያ :- መጋቢት 4/2012፤ March 13/2020):- ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ በሀገረ ስብከታቸው ሥር ለሚገኙ ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት የዲሲ፣ የሜሪላንድ እና ቨርጅንያ ግዛት አስተዳዳሪዎች ባስተላለፏቸው ጥብቅ መመሪያዎች መሠረት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ማንኛውም ዝግጅቶች እና መርሐ ግብሮች እንዳይኖሩ፣ ቀድመው የተያዙም ቢኖሩ እንዲሰረዙ ባዘዙት መሰረት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱም ይህኑ መመሪያ ተግባራዊ ማድርግ ይገባቸዋል ብለዋል።

አጥቢያዎቻችን ቤተ ክርስቲያን ካላቸው የሕዝብ ቁጥር ብዛት እና ከኢትዮጵያዊ የሰላምታ ባህል አንጻር ለቫይረሱ መተላለፊያ መንገድ አስጊ ሁኔታዎች በመኖራቸው እግዚአብሔር ይህን ጊዜ እስኪያሳልፈው ድረስ በየቤታችን ሁነን በጾም እና ጸሎት ወደ ፈጣሪ ልመናችንን ማቅረብ ይኖርብናል ሲሉም አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል::

የዲሲ ሜሪላንድ እና ቨርጂኒያ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ባወጧቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዎጆች እንደተመለከተው ትምህርት ቤቶች፣ ሙዚያሞች እና ሕዝብ በርከት ብሎ የሚሳተፍባቸው ስፖርታዊ ክንውኖች ለጊዜው እንዲዘጉ ተወስኗል።

ውሳኔው በሌሎች የአሜሪካ ስቴቶችም በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ዝርዝር መረጃዎች በየካውንቲው ድረ- ገጾች እና መገናኛ ብዙኅኖች የሚገለፅ መሆኑን እና በየጊዜው መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል።

Comments are closed.