በኦሮሚያ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንጠል ከሚሠሩ ሰዎች የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ገለፁ

(አደባባይ ሚዲያ፤ የካቲት 3/2012 ዓ.ም፤ Feb. 11/2020)፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምዕራብ አርሲ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ከአደባባይ ሚዲያ ጋር በኦሮምኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች ባደረጉት ቃለ ምልልስ «የግድያ ዛቻና ማስፈራሪያ» እንደሚደረግባቸው አስታወቁ።

ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በኦሮምኛ ቋንቋ የተለያዩ አገልግሎቶችን በሰጡባቸው በወለጋ እና አሁንም በሚያገለግሉበት በምዕራብ አርሲ ፖለቲካን እና ሃይማኖትን የደባለቁ ሰዎች በስልክና በተለያየ መንገድ እንደሚዝቱባቸው ለአደባባይ ሚዲያ አስረድተዋል። «በአባቶቻችን ላይ ቀድሞ የደረሰው እንጂ እኛ ላይ አዲስ የመጣ አይደለም» ያሉት ብፁዕነታቸው ማስፈራሪያውና ዛቻው ከሥራቸው እንደማያግዳቸው ገልጸዋል።

ስለ ጉዳዩ በደንብ የሚያውቁ ሌሎች ምንጮች እንዲህ ያለውን ማስፈራሪያ ያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች አሁን «በኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት» በሚባለው ቡድን ዙሪያ ያሉ ፀረ ቤተ ክርስቲያን እና ፀረ ኢትዮጵያ ሰዎች መሆናቸውን ነግረውናል። ከብፁዕነታቸው በተጨማሪ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልም ተመሳሳይ የመግደል ዛቻና እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንዳለ ይታወቃል።

ከብፁዕ አቡነ ሄኖክ ጋር ያደረግናቸውን የአማርኛ እና የኦሮምኛ ቃለ ምልልሶች ከሰሞኑ እናቀርባለን።

Comments are closed.