በኦሮሚያ ቤተ ክርስቲያንን ለማጠናከር ያለመው ጉባዔ በሚሌኒየም አዳራሽ ተካሔደ

(አደባባይ ሚዲያ፣ አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5/2012 ዓ.ም)፡- “ቤተ ክርስቲያን ሆይ፥ ፀሐይሽ አትጠልቅም” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ ታኅሣሥ 5/2012 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ ተካሒዷል። በአገልጋይ ዕጦት የተዘጉ፣ በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጥቃትና ተጽዕኖ ሥር ያሉ ሦስት የኦሮሚያ አህጉረ ስብከት አብያተ ክርስቲያንን ለማስከፈትና ለማጠናከር እንዲሁም ገቢ ለማሰባሰብ እና በሆሮጉድሩ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ከ800 በላይ የገጠር አብያተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማጠናከር ያለመው ጉባኤው ከ40ሺህ ያላነሱ መግቢያ ትኬቶች መሸጡን ምንጮቻችን ገልጸውልናል።

ከ3ቱ አህጉረ ስብከት ጠቅላላ አብያተ ክርስቲያን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ካህናትና መምህራን የሌላቸው በዓመት አንዴ እንኳ የማይቀድስባቸውና ስብከተ ወንጌልም የማይካሔድባቸው መሆናቸውም ተገልጿል። ይህንንም ለመቅረፍ ለእያንዳንዳቸው የሚያስፈልጋቸው ወርኀዊና ዓመታዊ የድጋፍ መጠን በጥናት መለየቱ የታወቀ ሲሆን የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎችና በጎ አድራጊዎች በሚችሉት መርጠው እንዲራዱ የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጠይቀዋል ሲል ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚዘግበው ሐራ ተዋሕዶ ድረ ገጽ ዘግቧል። ካህናትንና መምህራንን በብዛት ለማሠልጠን እንዲሁም ገቢ ለማስገኘት፣ በነቀምት የሀገረ ስብከቱ የልማት ይዞታ ላይ ለመገንባት የታቀደው ባለ ሰባት ወለል ሁለ-ገብ ዘመናዊ ሕንፃ ዲዛይን፣ በጉባኤው ላይ ቀርቦ ማብራሪያ ይሰጥበታል ያለው ድረ ገፁ ጸሎተ ምሕላ፣ ስብከተ ወንጌል፣ የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ፈተና የሚተነትኑ ቃለ ተዋስኦዎች፣ የጉባኤው መርሐ ግብሮች ይሆናሉ፣ በባለ ሙያዎችና በአህጉረ ስብከቱ ምእመናን የሚቀርቡ ገለጻዎችም ተካተዋል ተብሏል።

ዓላማውን የሚደግፉ በሙሉ ወደ ሚሌኒየም አዳራሽ በመሔድ የዚህ ታሪክ አካል እንዲሆኑ አዘጋጆቹ ተይቀዋል።

Comments are closed.