በምሥራቅ ወለጋ በአማራ ብሔረሰብ አባላት ላይ አደጋ እንዳንዣበበ እየተገለፀ ነው

(አደባባይ ሚዲያ):- OMN ዛሬ ሕዳር 28/2012 ዓ.ም በኦሮምኛ ባቀረበው ዜና “በ1998 ዓ.ም ከአማራ ክልል መጥተው በምሥራቅ ወለጋ ጉደያ ወረዳ የሠፈሩ የአማራ ተወላጆች ስጋት ሆነውብናል ሲሉ የአካባቢው የኦሮሞ ማኅበረሰብ አቤቱታ አቀረቡ” ሲል የሠራው ዘገባ በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን ይጠቁማል ሲሉ የአደባባይ ሚዲያ ባለሙያዎች ገለፁ::

ባለሙያዎቹ እንደጠቀሱት ከሆነ የOMN ዘገባ “ሠፋሪዎቹ” የሚሏቸው አማሮች የሠሯቸው የሚከተሉት ወንጀሎች ናቸው ብሎ ያቀረበው ዘገባ ብሔረሰብ ላይ ያነጣጠረ አደጋ እየመጣ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።

“ሁሉም የጦር መሣሪያ ታጥቀዋል። ሴቱም ወንዱም ታጥቋል። ገበያ ሳይቀር መሣሪያ ታጥቀው ነው የሚመጡት። የቦታውን የኦሮሞ ታሪካዊ ስም ወደአማርኛ ቀይረዋል። የይዞታ ቦታቸውን እያስፋፉ ነው። የኦሮሞን መሬት እየወረሩ ነው” በሚል በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርቅ ላይ የቀረበው ዘገባ በአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አደጋ ለመጣል ያሰበ አካል እንዳለ ማሳያ ነው ሲሉ የአደባባይ ምንጮች ይገልጻሉ።

“የወረዳው አስተዳደርም የመሣሪያ ምዝገባ ማድረጉን ገልጾ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ተመዝግቧል ብሎ እንደማያምን ጥርጣሬ እንዳለው” በOMN መገለጹ የአካባቢው መንግሥታዊ አስተዳደር ማንነት ላይ ያነጣጠር ጥቃት ሲጀመር የነዋሪውን ደኅንነት ላያስጠብቅ ይችላል የሚል ሥጋት ላይ የሚጥል መሆኑን የአደባባይ ወቅታዊ ጉዳዮችን ተከታታይ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ይህ አካሄድ ሕዝብን ለግጭት ቀድሞ የመቀስቀስ፣ “ሠፋሪ” ያሉትን የአማራ ህዝብ ለቀጣይ ጥቃት የማጋለጥ እና የእልቂት ዋዜማ እንደሚመስል፣ የማንመልሰው ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከማዘንና ከማልቀስ በፊት ችግሩ ከመከሰቱ ቀድሞ የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ አስጠንቅቀዋል።

Comments are closed.