ጣሊያን ሰልፍ አስተናግዳለች

(አደባባይ ሚዲያ):- በ26/03/12ዓም በትላንትናው ዕለት በጣልያንና በአካባቢው ሀገረ ስብከት የተከናወነው የሮማው መንፈሳዊ ሰልፍ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሰላም ተጠናቋል።

ሰልፉ የተጠራው በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በአውሮፓ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች በአንድ ላይ በመሆን በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በተያዘለት ቀጠሮ መሠረት ነው። ሰልፉ ከጠዋቱ በአራት ሰዓት በሮም ፖርላሜንቶ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ተጀንሯል። ምንም እንኳን የሥራ ቀን ቢሆንም ሰልፉ ላይ ከበቂ በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። ከሚላኖ፣ ከፖርማ፣ ከኡዲኒ፣ ከፍሬንዜ፣ ከሮማ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመሆን 10 ካህናት እና አባቶች በመገኘት በጸሎተ በወንጌል አስጀምረዋል።

አባቶች የማጽናኛ ቃልና ምክር ለሕዝብ በመስጠት፣ በጋራ ዝማሬ በመዘመር፣ በጣልያንኛ ቋንቋ የተዘጋጀ የአቋም መግለጫ እና የተለያዩ መፈክሮች በህብረት አሰምተዋል። የጣልያን ፓርላማ ጽ/ቤት ፊት ለፊት የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ቀጥታ ወደ ፓርላማው ጽ/ቤት በመግባት በጣልያንና በአካባቢዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የተጻፈውን ደብዳቤ በተወካዮች በኩል ለፓርላማው ጽ/ቤት አቅርበዋል።

ከደብዳቤው በተጨማሪ ደብዳቤውን ሊሰጡ የገቡ ተወካዮች በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በቃል በማብራራት አስረድተዋል። ጽሕፈት ቤቱም በአፋጣኝ ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳውቅ ገልጾ ተጨማሪ ቀጠሮ ለመያዝና የጉዳዩን ሂደት አፈጻጸም ለማስረዳት የቀጠሮ ቀን እንደሚያሳውቅ በመግለጽ ተወካዮችን በአክብሮት ሸኝቷል።

ይህንንም የፓርላማው ጽሕፈት ቤት ቆይታ በሰላማዊ ሰልፍ ለተገኙት ካህናትና ምእመናን ተገልጾላቸዋል። ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በሰልፉ ላይ የተያዘው መርሐ ግብር ሁሉ በተያዘው ሰዓት በጸሎት እንደተጀመረ በጸሎት ተዘግቶ በሰላም ተጠናቋል።

Comments are closed.